ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል
አዲሰ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይከናወናል፡፡
የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ስለጨዋታው ያላቸውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳየ አራጌ ፥ ዝግጅታችን ጥሩ ነው፤ ደርቢ ሲሆን ስሜቱ ከበድ ይላል ነገር ግን አንደማንኛውም ጨዋታ እንደሁልጊዜው ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
ጉዳትን በተመለከተ አጠቃላይ ሪፖርት ገና ነው ያሉት አሰልጣኙ ፥ የተሻለ ነገር ለማድረግ ወደሜዳ እንገባለን ፤ ከፍተኛ ስሜት በሚፈጠርበት የሸገር ደርቢ ሁላችንም ከስሜት መውጣት ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የአጨዋወት መንገዳችን ተከትለን ጨዋታውን በመቆጣጠር የተሻለ እንቅስቃሴና ውጤት ይዘን ለመውጣት በስነ ልቦና ተዘጋጅተናልም ብለዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ፥ ከቡና ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀናል ፤ ሆኖም ለጨዋታው እኔም ቡድኔም ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡
ከሶስት ተጫዋቾች ውጭ በቡድናቸው ሌላ ጉዳት አለመኖሩን የተናገሩት ዋና አሰልጣኙ ፥ እንደተለመደው ጨዋታው እስኪጠናቀቅ ደጋፊዎች ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ዛሬ 9 ሰዓት የሚደረግ ሲሆን ፥ የመግቢያ በሮች ከ 6 ሰዓት ጀምሮ ከፍት እንደሚሆኑ ተመላክቷል፡፡