Fana: At a Speed of Life!

በከፍተኛ ትምህርት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚካሄድ ወርክ ሾፕ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ትምህርት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር ላይ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ወርክ ሾፕ ተከፍቷል፡፡

በመላ አገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ፕሬዚዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የልማት እቅድ እና ፕሮጀክቶችን የሚመሩ ኃላፊዎች በተከፈተው ወርክሾፕ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡

በወርክ ሾፑ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የ16 ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና ሌሎች ኃላፊዎችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ፕሮጀክቱን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክር ፍጹም አሰፋ ያስጀመሩት ሲሆን÷የከፍተኛ ትምህርት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር መመሪያ ዋና አላማ ሐብትና ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን በፍጥነት ወደ እድገት እና ልማት ለመለወጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ያለውን ደካማ የመንግስት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰው÷ በተከፈተው መድረክ የሚገኙ ግብዓቶችን የመንግስት ኢንቨስትመንት መመሪያን ለማዳበር የሚረዳ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው÷ ባለፉት ዓመታት በአገራችን ከተፈጠሩ ክስተቶች አንጻር የመንግስትን የገንዘብ አጠቃቀም በጥንቃቄ መያዝ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይ በዓለማችን የሚከሰቱ ለውጦችን ከግምት ለማስገባት በትምህርት ዘርፍ ጥራትን አስጠብቆ ግብዓቶችን በአግባቡ ለመጠቀም የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር ጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር አስፈላጊነትን አስመልክቶም ማብራሪያ የሰጡት ደግሞ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ ናቸው፡፡

በከፍተኛ ትምህርት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸውን ጉዳዮችም ያነሱ ሲሆን÷ በቀጣይ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሳተፉ መግለጻቸውንም ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.