Fana: At a Speed of Life!

የሜቴክ የቀድሞ የስራ ሀላፊዎች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ በነበሩ በሜቴክ የቀድሞ የስራ ሀላፊዎች ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁሩንዲ እና ሌተናል ኮሎኔል አሰፋ ዮሐንስን ጨምሮ በሶስት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው፡፡
ተከሳሾች ስልጣንን ያላግባብ በመገልገል፣ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት እና የህዝብ እና የመንግስትን ጥቅም የጎዳ ተግባር በመፈጸም የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1) (ሀ)፣ 33 እና 407 (1) (ሀ)፡ (2) ፡(3) ፤ 411 (1) (ሀ)(ሐ) እና (3) ላይ የተመለከተውን በመተላለፋቸው ነው ክስ ተመስርቶባቸው ጥፋተኛ የተባሉት።
ተከሳሾቹ የቀድሞው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮርፖሬት ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁሩንዲ߹ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ እና የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ክንደያ ግርማይ አንዲሁም በቻይና ህዝባዊ ሪፑብሊክ ቲምስ ኢንተርናሽናል (ሆ.ኮ) ኩባ. ሊሚትድ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትና ያልተያዙት ዩዋን ሃን ናቸው ።
ተከሳሾች በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ በሃላፊነት ደረጃዎች ላይ የመንግስት ሰራተኞች ሆነው ሲሰሩ ለጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ማምረቻ ፋብሪካ የሚያገለግል ግዥ ለመፈጸም ከጨረታ ውጪ እና በመመሪያው የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ግዥዉን ያለ ግልፅ ጨረታ መፈጸማቸው ተጠቅሷል።
በዚህም በውሉ የተመለከተው የስራ አፈፃፀም የባንክ ዋስትና ባልቀረበበት ሁኔታ ክፍያ በመፈፀም እንዲሁም ከጠቅላላ የውሉ ዋጋ 10 በመቶ በዋስትና መልክ መያዝ የነበረበትን 5ሚሊየን 564 ሺህ ዶላር ገንዘብ ባለመያዝ፣ ስራው ሣይጠናቀቅ ጠቅላላ ክፍያው ሙሉ በሙሉ እንዲከፈል በማድረግ እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ ስራውን ሣይጨርስ ፕሮጀክቱ ገና በ63 ነጥብ 14 በመቶ ደረጃ ላይ እያለ በራሱ ጊዜ አቋርጦ በመውጣቱ፥ ላልተሰራ ሥራ 422 ሚሊየን 791 ሺህ 908 ነጥብ 47 ብር አላግባብ በመክፈል መንግስት ፕሮጀክቱን ለማጠናቅቅ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት ጋር በገባው ውል መሰረት አላግባብ 6 ሚሊየን 400 ሺህ ዶላር ተጨማሪ ወጪ በመዳረጉ፤ ስልጣንን አላግባብ በመገልገል፣ የሙስና ወንጀል በመፈፀም በሚሉ በርካታ ክሶች በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል ፡፡
ካልተያዘው 4ኛ ተከሳሽ ውጭ ያሉት ሌሎች 3 ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ዝርዝር የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በማስረዳቱና ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበባቸውን ክስና ማስረጃዎች ያላስተባበለ መሆኑን የተቸው ችሎቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ የጥፋተኝነት ፍርድ መሰጠቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.