Fana: At a Speed of Life!

“አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ” የምስራቅ አፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ እንደሚከፍት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ” የምስራቅ አፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

“አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ” (ኢ- ትሬድ ግሩፕ) የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራትን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የንግድ ልውውጥን ለማሳለጥና በጋራ ለመስራት የተቋቋመ ኩባንያ ነው ተብሏል።

የኩባንያው ዋና መስሪያ ቤት ሩዋንዳ ኪጋሊ ሆኖ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እና የንግድ ተቋማትን በማቀፍ የአህጉሩን ኢኮኖሚ ለማሳደግና የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ጭምር እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡

በዕቅዱ መሰረት ኩባንያው በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ከ600 ሺህ በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ የስራ መስኮችን ይፋ የማድረግ ዓላማም አለው።

የ”ኢ- ትሬድ ግሩፕ” የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉዓለም ስዩም ÷ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ሕዝብ ያላትን አፍሪካ ለማልማትና የገበያ ዕድል ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

አገራቱ የንግድ ትስስራቸውን ከፍ ቢያደርጉ ዓመታዊ የምርት ምጣኔያቸውን ከማሳደግ ባለፈ አቅርቦትና ፍላጎታቸውን ለማጣጣም ትልቅ ዕድል የሚፈጥርላቸው ይሆናልም ነው የተባለው።

በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የሚመረቱ ቁሳቁሶች ሰፊ ገበያ እንዲያገኙና የኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ያደርጋልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ18 የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ተወዳድራ የአፍሪካ ኢ- ትሬድ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ መቀመጫ ሆና መመረጧን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለዋል።

ኩባንያው በተለይ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፉ ውጤታማነት መደላድል ለመፍጠር ከአፍሪካ አገራት መንግስታት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የ“አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ” እስካሁን ለምዕራብ አፍሪካ አገራት በጊኒ፤ ለደቡባዊ አፍሪካ አገራት ደግሞ በስዋቲኒ ቅርንጫፎቹን የከፈተ ሲሆን ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ደግሞ በአዲስ አበባ ለመክፈት እንደተዘጋጀም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.