Fana: At a Speed of Life!

ስፖርት ዲሲፕሊን አክባሪ መሆንን እንደሚጠይቅ ሁሉ፥ አገርን ለመለውጥም ለህግና ስርዓት የምንገዛ መሆን አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፖርት ዲሲፕሊን አክባሪ መሆንን እንደሚጠይቅ ሁሉ፥ አገርን ለመለውጥም ህግና ስርዓትን የምናከብር፥ለህግና ስርዓት የምንገዛ መሆን አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስገነዘቡ።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ያዘጋጀው 4ኛው የኢቢሲ-ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ሽልማት ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ ስፖርት ለግልም ለሀገርም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፥ ስፖርትና ሀገር የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች እንዳሉም አብራርተዋል።

ስፖርት የግልም የቡድንም ስራ እንደመሆኑ የግል ትጋትን፣ ብቃትንና ችሎታን እንዲሁም የጋራ ውጤት ማስመዝገብን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

በሀገርም እንዲሁ እያንዳንዱ ግለሰብ በተሰጠው ኃላፊነትና ስራ በታማኝነት በማገልገል ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅበታል ብለዋል።

እንዲሁም ዜጎች በጋራ ተደምረውና ተንሰላስለው የሀገራቸውን መፃኢ ሁኔታ እንዲወስኑ ያስችላል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

እንደስፖርት መስክ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው በየተሰማራበት መስክ ሲሰራ እራሱን ብቻ የሚጠቅም ሳይሆን አገሩንም የሚጠቅም መሆን እንዳለበት ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያመላከቱት፡፡

ስፖርት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅና ተጨማሪ ስልጠና፣ ቁርጠኝነትና ጥበብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ፥ የሀገር ግንባታም እንደዚሁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አገርና ስፖርት በስራ፣ በልምምድ፣ በትምህርትና በቴክኖሎጂ ተሳስረው እንዲሄዱ የእውቀትን ዋጋ መገንዘብ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

ስፖርት ዲሲፕሊን አክባሪ መሆንን እንደሚጠይቅ ሁሉ፥ አገርን ለመለውጥም ህግና ስርዓትን የምናከብር፥ለህግና ስርዓት የምንገዛ መሆን አለብን ሲሉም በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡

ይህ ትውልድ የላቀ ስራ ሰርተው ዛሬ የተሸለሙትን ሰዎች ሲመለከት ነገ ተሸላሚ ለመሆን መትጋት፣ ዲስፒሊን አክባሪ መሆንና ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተመሳሳይ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክትም፥ “በመካከላችን ያሉትን በርካታ ጀግኖች መዘንጋት የለብንም፤ ነባሮቹን በማድነቅና ተምሳሌት በማድረግ አዳዲሶችን በመከባከብ ብዙ ጀግኖችን ለመፍጠር መትጋት አለብን” ብለዋል።

ስፖርት የግል ጥቅምን ከማስፈን ባሻገር የሀገር ገጽታ ግንባታን ይደግፋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስፖርት እንደ አንድ ሀገር የማያቋርጥ እና ተጨማሪ ጥረት እና ጠንክሮ መሥራትን እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

የስፖርት ጀግኖቻችንን ስኬት፣ ታታሪነት እና ውጤታቸውን ስናከብር እንደ ሀገር ስፖርቱ የሚያሳየንን ትምህርት እናስተውል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለዛሬ ተሸላሚዎችም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተገኙበት በዚሁ የሽልማት ሥነ ሥርዓት በሁለቱም ፆታዎች በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ እና በአሰልጣኞች ምድብ የተካሄደው ውድድር የየዘርፉ አሸናፊዎች ታውቀዋል።

በዚህም መሰረት የ2013 ዓ.ም 4ኛው የኢቢሲ-ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ሽልማት በሴቶች እግር ኳስ ዘርፍ ምርጥ ተጫዋች ሎዛ አበራ ሆና ተመርጣለች።

በሴቶች አትሌቲክስ ዘርፍ ደግሞ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ አሸናፊ ሆና ተመርጣለች።

በሴቶች እግር ኳስ የአሰልጣኝ ዘርፍ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አሸናፊ ሆኖ ሲመረጥ፥ በአትሌቲክስ አሰልጣኞች ዘርፍ ደግሞ አሰልጣኝ ተሾመ ከበደ ተመርጧል።

የውድድሩ ልዩ ተሸላሚ አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ሆና መመረጧም ታውቋል።

በወንዶች እግር ኳስ የአሰልጣኞች ዘርፍ አሸናፊ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ሆኖ ተመርጧል።

በወንዶች አትሌቲክስ ዘርፍ አሸናፊ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሆኖ ተመርጧል።

በወንዶች እግር ኳስ ዘርፍ አሸናፊ ተጫዋች አቡበከር ናስር ሆኖ ተመርጧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.