በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳድረው በማሸነፍ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ያገኙ ወጣት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳድረው በማሸነፍ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ያገኙ ወጣት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ነው ለ15 የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎችና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ሽልማት የሰጠው።
መድረኩ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች እና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የእርስ በርስ ትስስር እንዲፈጥሩ ታልሞ የተዘጋጀ ሲሆን÷ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አሸናፊዎች ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ÷ መንግስት ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የሚደገፉበትን ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሊ ቢዮንግ ኋ÷ ኢትዮጵያ ለኢኖቬሽን ዘርፍ ስራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት ኤጀንሲው ይደግፋል ብለዋል፡፡
ከአይ ሲ ቲ፣ ከግብርና፣ ከማምረቻ ዘርፍ፣ ከቱሪዝም፣ ከማዕድን እና ከዲጂታል ዘርፎች የተውጣጡ 15 የቴክኖሎጂ አበልጻጊ ተሸላሚዎች በንግድ እና ቴክኒካል ጉዳይ ስልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል።
በበተሰጣቸው ስልጠና መሰረትም ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶችን ተወዳድረው በማሸነፍ ከ25 ሺህ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚልየን ዶላር ፕሮጀክች ፈንድ አሸንፈዋል፡፡
በተደረገላቸው እገዛና ድጋፍ ባስገኙት ውጤትም ተመዝነው ከ200 በላይ የስራ እድዕል ለፈጠሩና ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ሀብት ማፍራት የቻሉ አምስት ድርጅቶች ከ1 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ ዶላር መሸለማቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡