Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማዕድ አጋራ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የደቡብ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ “ሆፕ ፎር ጀስቲስ”ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመቀናጀት የፋሲካ በዓልን በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚያሳልፉ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር አከናወነ።

በወላይታ እና ሆሳዕና አካባቢ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚገኙ ወላጅ አልባ ሕፃናት ነው ማዕድ የማጋራት እና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ መርሃ-ግብር የተከናወነው።

በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ጎዳና ሕይወት የወጡ ሕፃናትን ሥነ -ልቦና ለመገንባት እና ቀጣይ ሕይወታቸው ያማረ እንዲሆን በተለያዩ ጊዜያት የሚከበሩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ባይዳ ሙንዲኖ ተናግረዋል።

የሕፃናቱን ሥነ-ልቦና ለመገንባትና ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የሚደረገው ድጋፍ በበዓላት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ዘወትር መለመድ ያለበት ተግባር እንደሆነም ጠቁመዋል።

በወላይታ ዞን የሆፕ ፎር ጀስቲስ ግብረ ሠናይ ድርጅት ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሰላሙ ይገዙ መርሃ ግብሩ በተለያዩ ምክንያቶች ጎዳና የወጡ ሕፃናትን ለመታደግና በበዓላት ወቅትም እንዳይከፋቸው ማዕድ ለማጋራት የተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ማዕድ በማጋራት መርሃ ግብር ላይ የተገኙ ሕፃናትም ÷ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውንና በቀጣይም የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በማቴዎስ ፈለቀ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.