የአዋሽ 7 ኪሎ – ጭሮ የማስተላለፊያ መስመር ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ስራ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዋሽ 7 ኪሎ – ጭሮ የማስተላለፊያ መስመር ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ስራ መጠናቀቁን በኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ ሪጅን ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የጥገና ሥራ አስተባባሪ አቶ ተካልኝ ጉተማ እንደገለጹት÷ ኢንሱሌተሮቹን መቀየር ያስፈለገው የማስተላለፊያ መስመሩ በ1955 ዓ.ም ከቆቃ ኃይል ማመንጫ ጋር ተገንብቶ ረጅም ዓመት ያገለገለ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
በአገልግሎት የተነሳ ኢንሱሌተሮቹ መሰባበር በመጀመራቸው የኢሌክትሪክ ኃይል እንዲቆራረጥና በሀገሪቱ ኃይል ስርጭት ላይም መስተጓጎል እንዲፈጠር ማድረጉን አስታውሰዋል።
ለወራት ሲከናወን በቆየው የኢንሱሌተሮች ቅየራ ሥራ በ262 ምሰሶዎች ላይ 786 ኢንሱሌተሮችን በአዲስ የፕላስቲክ ኢንሱሌተሮች ሙሉ በሙሉ መቀየራቸውን አስታውቀዋል።
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ በበኩላቸው÷ ሥራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ የጭሮ ማከፋፈያ ጣቢያ ከባቡር መስመር ላይ ሲጠቀም ቆይቷል ብለዋል፡፡
ቅየራው የሀገሪቱን ግሪድ ከማስተካከል ባለፈ በምዕራብ ሐረርጌ የሚኖረውን የከፍተኛ መስመር ኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚቀንስ መሆኑም ተመላክቷል።
የቅየራ ሥራው የተከናወነው በ132 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ላይ ሲሆን÷ ከማከፋፈያ ጣቢያው በኋላ በ66 ኪሎ ቮልት እየተገለገሉ ያሉት የበዴሳና ገለምሶ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለመቀነስ ተመሳሳይ ስራ እንዲከናወን አቶ ጋሻው አሳስበዋል።
ሥራው በተቋሙ የጥገና ባለሙያዎች እና 300 ሺህ ብር በሆነ ወጪ መከናወኑን ከኤሌክትሪክ ሀይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!