Fana: At a Speed of Life!

በምዕራብ እና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ እንዳይሳለጥ ባደረጉ ከ1 ሺህ 425 በላይ ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ እና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ እንዳይሳለጥ ባደረጉ ከ1 ሺህ 425 በላይ ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ፡፡
የምዕራብ ሸዋ ዞን በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንቅፋት ሆነዋል በተባሉ ከ700 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ ይማሙ፥ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በዞን እና በወረዳ ደረጃ 2 ሺህ 823 ቅሬታዎች እንዳሉ መለየታቸውን ጠቁመው፥ ከእነዚህ ውስጥም 644 ያህሉ መፍትሄ ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ጋር በተያያዘ እስካሁን በተወሰደ እርምጃም 42 ሠራተኞች ከሥራ መሰናበታቸውን ገልጸው፥ 166 ሠራተኞች ደግሞ በደመወዝ መቀጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 67 የወረዳ አመራሮች እና 26 በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የመሠረታዊ አመራሮች እንዲሁም 22 ሠራተኞች ከቦታ መነሳታቸውን ነው የገለጹት።
በተመሳሳይ ለ91 ሠራተኞች የጽሑፍ እና ለ287 ሰራተኞች ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አቶ ተካልኝ ተናግረዋል፡፡
በተወሰደው እርምጃም 1 ሚሊየን 504 ሺህ 606 ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ መደረጉን ምክትል አስተዳዳሪው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በዞን ደረጃ በሙስና የተጠረጠሩ ሰባት ሠራተኞች በሕግ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ መግለጻቸውን ከኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ በምሥራቅ ሸዋ ዞን የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳይሳለጥ ባደረጉ 725 አመራሮች እና ባለሙያዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
እርምጃ የተወሰደባቸው ከቀበሌ እስከ ዞን ያሉ አመራሮች እና ባለሙያዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.