Fana: At a Speed of Life!

በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራና በውስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ሀገሪቱን የማተራመስ እኩይ ውጥን በፍፁም እንደማይሳካ መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራና በውስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ሀገሪቱን የማተራመስ እኩይ ውጥን በፍፁም እንደማይሳካ መንግስት ገለፀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ፥ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል ሰላት በደማቅ ሁኔታ በመካሄድ በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል።
አብዛኛው ሰላም ወዳድ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረጉት ተሳትፎና ከፀጥታ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ያሳዩት ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅና የሚበረታታ ነውም ብሏል መግለጫው።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ካጋጠመው ረብሻ ጋር ተያይዞ ግጭቱን ወደ ደቡብ ክልል ወራቤ ከተማና ወደ ሌሎች አካበቢዎች በማስፋፋት ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሙከራ ማድረጋቸው ያስታወሰው መግለጫው፥ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰሞኑን የፀረ-ኢትዮጵያ አቋሞቻቸውን በመግለፅ ቀጣይ ሊፈጥሩት ስላሰቡት ሁከት በአደባባይ ሲገልፁ ሰንብተዋል ብሏል፡፡
ይህንኑ እኩይ ዓለማቸውን በዛሬም በአዲስ አበባ የታላቁ ዒድ ሰላት ላይ ለመተግበር ሙከራ ቢያደርጉም በንብረት እና በፀጥታ ሃይሎች ላይ ከደረሰው መለስተኛ ጉዳት ውጭ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ወዳድ አማኞችና በፀጥታ ሃይሎች ቅንጅት የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅዱ መክሸፉን ገልጿል።
በቀሪዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው የታላቁ የኢድ አልፈጥር በዓል ሰላት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዶ በሰላም ተጠናቋልም ነው ያለው።
“መላው ህዝባችን የታሪካዊ ጠላቶቻችንና በውስጣችን የሚገኙ የተላለኪዎቻቸውን እኩይ ሴራዎች ተገንዝቦ ፅንፈኝነትንና መገፋፋትን በቁርጠኝነት በመታገል ህብረ ብሄራዊ አንድነቱን ማረጋገጥ አለበት” ብሏል መንግስት፡፡
መንግስት በፅንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃም አጠናክሮ ይቀጥላል ያለው መግለጫው፥ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች በማወቅም ይሁን ባለመወቅ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን አካላት አንድ በአንድ በመልቀም መንግስት የጀመረውን ህግና ስርዓት የማስከበር ብሎም የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
ይህንን ተግባር ለማፈፀም መንግስት ሙሉ ቁርጠኝነትና ጠንካራ አቅም እንደላውም ነው ያረጋገጠው።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራና በውስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ውጥን በፍፁም አይሳካም!
በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል ሰላት በደማቅ ሁኔታ በመካሄድ በሰላም ተጠናቋል፡፡ አብዛኛው ሰላም ወዳድ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረጉት ተሳትፎና ከፀጥታ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ያሳዩት ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው፡፡
ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማተራማስና ለማፍረስ እንደ መሳሪያ ከሚጠቀሙባቸው ጉዳዮች ውስጥ የለውጥ ሂደቱ ፈተና ሆነው የቀጠሉት የሃይማኖት ፅንፈኝነት፣ አክራሪነትና መንደርተኝነት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የውስጥ ባንዳዎች በሃይማኖት ሽፋን ከውጭ ኃይሎችና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተቀናጅተው ማህበራዊ ትስስሮቻችንን ለመበጣጠስ፤ በሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ለማድረግ እንዲሁም ከአንድነት ይልቅ መበታተንና መከፋፈል እንዲፈጠር አልመው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ካጋጠመው ረብሻ ጋር ተያይዞ ግጭቱን ወደ ደቡብ ክልል ወራቤ ከተማና ወደ ሌሎች አካበቢዎች በማስፋፋት ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሙከራ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰሞኑን የፀረ-ኢትዮጵያ አቋሞቻቸውን በመግለፅ ቀጣይ ሊፈጥሩት ስላሰቡት ሁከት በአደባባይ ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡ ይህንኑ እኩይ ዓለማቸውን በዛሬም በአዲስ አበባ የታላቁ ዒድ ሰላት ላይ ለመተግበር ሙከራ አድርገዋል፡፡
በሰማዕታት ሃውልትና በመስቀል አደባባይ በንብረት እና በፀጥታ ሃይሎች ላይ ከደረሰው መለስተኛ ጉዳት ውጭ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ወዳድ አማኞችና በፀጥታ ሃይሎች ቅንጅት የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅዱ ከሽፏል፡፡ በቀሪዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው የታላቁ የኢድ አልፈጥር በዓል ሰላት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዶ በሰላም ተጠናቋል፡፡
መላው ህዝባችን የታሪካዊ ጠላቶቻችንና በውስጣችን የሚገኙ የተላለኪዎቻቸውን እኩይ ሴራዎች ተገንዝቦ ፅንፈኝነትንና መገፋፋትን በቁርጠኝነት በመታገል ህብረ ብሄራዊ አንድነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡
መንግስት በፅንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች በማወቅም ይሁን ባለመወቅ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን አካላት አንድ በአንድ በመልቀም መንግስት የጀመረውን ህግና ስርዓት የማስከበር ብሎም የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይህንን ተግባር ለማፈፀም መንግስት ሙሉ ቁርጠኝነትና ጠንካራ አቅም እንደላው በዚህ አጋጠሚ ማረጋገጥ እንወደለን፡፡
ዘመን የማይሽረውን የህዝባችንን አንድነትና መተባበር በማጎልበት ሁለም ሰው ያለ ልዩነት ሃይማኖትን፣ ብሄርንና መንደርተኝነትን ማእከል ያደረገውን አክራሪነትና ፅንፈኝነትን የመወጋት ዘመቻን በፅናት መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራና በውስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ውጥን መቼም ቢሆን አይሳካም!
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም የዒድ አልፈጥር በአል እንዲሆን እንመኛለን!
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.