Fana: At a Speed of Life!

በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ጥፋቶች ሊወገዝ እና ጥፋተኞች ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል- የጋምቤላ ክልል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ የሚከሰቱ ጥፋቶች ሊወገዙ እና ጥፋተኞች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል አሳሰበ፡፡

ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች የተስተዋሉ ሐይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሀገሪቱን አንድነትና የህዝቡን አብሮነት የሚሽረሽሩ እንቅስቃሴዎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዌይ ጆክ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ÷ የክልሉ ህዝብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት ሁሉም በየአካባቢው ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በዓሉን አክብሯል ብለዋል።

በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በሃይማኖት ሽፋን ሀገርን የማፍረስ ሴራ ያነገቡ ኃይሎች በቅርቡ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሙከራ እያደረጉ መሆኑን በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላትን ህብረተሰቡ በጋራ በመሆን ሊታገላቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ጥፋቶች ሊወገዙ እና ጥፋተኞች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በክልሉ በሰላም መከበሩን ጠቁመው፥ ይህ ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.