Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የሕዝብ አንድነትን በማጠናከር ሀገር የማሻገር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል አለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት እና ከሕብረተሰቡ ጋር ትስስሮችን በማጠናከር ሀገር የማሻገር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት እና ባሕል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የገመገመ ሲሆን ፥ በዚሁ ወቅትም ሚኒስቴሩ በስፖርት፣ በባሕል፣ በዕደ-ጥበብ፣ በኪነ-ጥበብ እና በሥነ-ጥበብ ዘርፎች ብዙ እንደሚጠበቅበት ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ፥ ኢትዮጵያን የመቻቻል፣ የአንድነት እና የሰላም እንዲሁም የአብሮነት እና የፍቅር ተምሳሌት አድርጎ ከማስቀጠል አኳያ፣ የኪነ-ጥበብ እና ስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እነዚህን ጉዳዮች ለማስቀጠል፣ በጥናት እና ምርምር የተደገፈ ፖሊሲ በመቅረጽ፣ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተናብቦ እና ተቀናጅቶ ሊሠራ እንደሚገባው መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

የባሕል እና ስፖርት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር እንዳልካቸው ሌሊሳ በበኩላቸው ፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት ከመፍጠር፣ የጠራ ዕቅድ ከማዘጋጀት እንዲሁም ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተናብቦ እና ተግባብቶ ከመሥራት አንጻር ክፍተቶች እንደሚታዩበት አመላክተዋል።

ግጭትን ለሚያበርዱ ባሕላዊ የእርቅ ሥነ-ሥርዓቶች አነስተኛ ቦታ መስጠት፣ ተተኪ እና አዳዲስ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በሚፈለገው ደረጃ አለማፍራት፣ ታሪክን እና ቋንቋን በጥናት እና ምርምር የማበልፀግ እና የማልማት ሥራዎች አጥጋቢ አለመሆን፣ ከሚኒስቴሩ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተጨማሪ ነገሮች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው ፥ የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን ቋንቋ እና ኪነ-ጥበብ ለማጎልበት፣ የዕደ-ጥበብ ምርቶችን እና ገበያ ለማስፋፋት፣ በባሕል ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ዓቅም ለማሳደግ፣ ሀገር-በቀል ዕውቀቶችን ለማልማት እንዲሁም ትውፊታዊ ሀብቶችን እና ማኅበራዊ ዕሴቶችን ለሕዝቦች ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ለማዋል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግብ ቀርጾ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ከቋሚ ኮሚቴው የተጠቆሙ ክፍተቶችን እና ድክመቶችን በግብዓትነት በመጠቀም፤ በሕዝቦች መካከል መቀራረብ እና አንድነት፣ መቻቻል እና ሰላም እንዲሁም የእርስ በርስ ትስስሩን የሚያጎለብቱ የኪነ-ጥበብ፣ የስፖርት እና የባህል ሁነቶችን ለማዘጋጀት፤ ከተጠሪ ተቋማት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተባብሮ እንደሚሠራ አቶ ቀጀላ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ምላሽ አስገንዝበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.