Fana: At a Speed of Life!

ለሥራ ፈላጊው ወጣት ሥራ ለመፍጠር ሚኒስቴሩ ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር መክሮ የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል – አቶ ንጉሡ ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሥራ ፈላጊው ወጣት ሥራ ለመፍጠር የሚሰሩ ጣቢያዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር መክሮ የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገለጹ።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከክልል እና ከተማ አስተዳደሮች የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች እና የቢሮ ኃላፊዎች ጋር በአዳማ ከተማ ያካሄደውን መድረክ ዛሬ አጠናቋል።

በመጀመሪያው ዙር ከሰባት ክልሎች ተወክለው የመጡ የጣቢያዎቹ አስተባባሪዎች እና ኃላፊዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ጣቢያዎቹ ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ የቁሳቁስ አለመሟላት፣ የስልጠናዎች አለመመቻቸት፣ የሠራተኞች ፍልሰት፣ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ማነስ እና የመሳሰሉት ችግሮች ተነስተዋል።

ውይይቱን የመሩት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፥ መድረኩ ለሥራ ፈላጊው ወጣት ሥራ ለመፍጠር የሚሰሩት ጣቢያዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመረዳት ሰፊ ዕድል ሰጥቷል ብለዋል።

ይህንንም ለመፍታት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በጣቢያዎቹ መካከል ካሉት የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አደረጃጀቶች ጋር ተመካክሮ የመፍተሔ አቅጣጫ የማስቀመጥ ድርሻውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ነቢሃ መሀመድ በበኩላቸው ፥ የአንድ ማዕከላት ጣቢያ አስተባባሪዎቹ ወጣቱን ከሥራ ጋር የሚያገናኙ እንደመሆናቸው የተነሱት ጥያቄዎች ግልፅ እና ለመፍትሔ የሚመቹ በመሆናቸው በአጭር እና ረጅም ጊዜ ከፋፍለን ምላሽ የሚያገኙበትን አቅጣጫ እንከተላለን ነው ያሉት፡፡

አክለውም ፥ አስተባባሪዎቹ የወጣቱ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ችግሮቹን ላይ ብቻ ከማትኮር ይልቅ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ለሁለት ቀናት የተካሄደው የመጀመሪያው መድረክ ሲጠናቀቅ፥ የሌሎች የክልል እና ከተማ አስተዳደሮች የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ አስተባባሪና ኃላፊዎችን በማሳተፍ በቀጣይ እንደሚካሄድ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.