ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በቀጣይ 60 ቀናት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ዝግጅት ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በቀጣይ 60 ቀናት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ዝግጅት ጎበኙ፡፡
አስተዳደሩ በአምስት ክፍለ ከተሞች በልዩ ሁኔታ የሚተገበሩ የ60 ቀናት ሰው ተኮር ተግባራትን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ይህን ተከትሎ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በልዩ ሁኔታ የሚሰራቸውን ሰው ተኮር ተግባራት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ይፋ አድርጎ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት ማሳኪያ የሚሆኑ የቦታ መረጣ ያለበትን ሁኔታ ከንቲባዋ የጎበኙ ሲሆን÷ ሁሉም ተግባራት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ማረጋገጣቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይ ለቤት ግንባታ፣ ለሸገር ዳቦ ፋብሪካና ማከፋፈያ፣ ለከተማ ግብርና፣ ለምገባ ማዕከላት እና ለሌሎች ተግባራት የተለዩ ቦታዎች የግንባታ ዲዛይናቸው በአብዛኛው የተጠናቀቀ በመሆኑ ወደ ግንባታ ስራ እንዲገቡም ከንቲባ አዳነች አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡