Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በሐረር ዓመታዊ የአቅመ ደካማ ወገኖችን የቤት እድሳት መርሐ ግብር አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ዓመታዊ የአቅመ ደካማ ወገኖች የቤት እድሳት መርሐ ግብርን በዛሬው ዕለት አስጀመሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን ዛሬ ያስጀመሩት የቤት እድሳት መርሐ ግብር፥ በዓለም የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የአለም ቅርስነት በተመዘገበው ጀጎል ውስጥ የሚገኝ በከፊል ፈርሶ በነበረ ቤት ነው፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፥ “በግንባታ ሂደቱ የምንጠቃማቸው ግብአቶችና ሌሎች የግንባታ ይዘቶች ቀደም ብሎ በተቀመጠው የጀጎል ቤት ግንባታ መመሪያ እና አሰራር የሚከናወን ይሆናል” ብለዋል።
ይኸውም ቤቱ ቀደም ብሎ የነበረውን ይዘትና ቅርጽ አግባብነት ባላቸው ግብአቶችና የግንባታ ሂደቶች የመመለስ ጉዳይ ይሆናልም ነው ያሉት።
በትናትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዓመታዊ የቤት እድሳት መርሐ ግብርን በአዲስ አበባ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገውን ዓመታዊ የቤት እድሳት መርሐ ግብርን ግለሰቦች፣ የንግድ ተቋማትና የመንግሥት ተቋማት ክረምት ከመግባቱ በፊት በአካባቢያችን ላሉ በርካታ ሰዎች ምቹ እና ሰብአዊ ክብርን መሠረት ያደረገ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ዓመታዊ ክንውን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውም የሚታወስ ነው፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.