Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ በጋራ እና በትብብር መስራት ይገባል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እና በአህጉር ደረጃ በጋራ እና በትብብር መስራት እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳሰቡ፡፡

የአፍሪካ የመከላከያ ኤታማዦር ሹሞች እና የደህንነት ኃላፊዎች 17ኛው መደበኛ ስብሰባ ለማዘጋጀት የልዩ ቴክኒካል ኮሚቴ የመከላከያ እና ደህንነት የባለሙያዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፥ ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ እና በአህጉር ደረጃ በጋራ እና በትብብር መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በምክክር መድረኩ የአፍሪካ ህብረት የፖሊሲ አካላት የሰላም እና የጸጥታ ውሳኔዎችን በተለይ የመከላከያ ደህንነት እና ደህንነት ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ (STCDSS) 13ኛ መደበኛ እና 3ኛ ድንገተኛ ስብሰባዎች የተካሄዱ የሰላም እና የጸጥታ ውሳኔዎች አፈፃፀም ተገምግሟል።

ካለፉት ስብሰባዎች ጀምሮ በኮሚሽኑ የተከናወኑ ቁልፍ ክንውኖችን የገለጹት የግጭት አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር አላሃጅ ሶርጆ ባህ÷ የሚመለከታቸው የሕብረቱ የፖሊሲ አካላት ቁልፍ የሰላም እና የደህንነት ውሳኔዎች አተገባበር ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሴኔጋል ሪፐብሊክ የጦር ኃይሎች ሜጀር ጄኔራል እና የባለሙያዎች ስብሰባ ሊቀ መንበር ማማዱ ጌዬ÷ በአህጉሪቱ እየደረሰ ያለውን የሽብር ጥቃት አውግዘዋል።

በስብሰባው የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት እና የቀጠናዉ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች የክልላዊ የግጭት መከላከል፣ አስተዳደር እና አፈታት ዘዴ ተወካዮችም ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.