በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ምርጫ እንዲካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአሶሳ ከተማ ውይይት አካሄደ፡፡
በቦርዱ የምርጫ ኦፕሬሽን ምክትል ማናጀር አቶ ብሩክ ወንድወሰን እንደገለጹት÷ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በክልሉ አንዳንድ የምርጫ ክልሎች አልተካሄደም።
ምርጫ ባልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ምርጫ ለማካሄድ ቦርዱ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ማወያየቱን ጠቅሰዋል፡፡
ቦርዱ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ካደረገ በኋላ ምርጫው እንዲካሄድ ለማድረግ ማቀዱን የጠቆሙት አቶ ብሩክ÷ በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ሁኔታ ዳሰሳ ጥናት ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የውይይቱ ዓላማም በሰነዱ ላይ ግብዓት በማሰባሰብ ለቀጣይ ስራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በውይይት መድረኩ የብልጽግና፣ እናት፣ አብን፣ ኢዜማ እና ሌሎችም ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ፖሊስ፣ ሠላም ግንባታ ጸጥታ ቢሮ እና የቦርዱ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡