በታንዛኒያ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ በእስር ላይ ላሉ ኢትዮጵያዊያን የጋራ መፍትሄ ለማፈላለግ ሀገራቱ ከስምምነት ደረሱ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የታንዛኒያ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የለውጥ ስራዎችን ጎበኘ፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይታቸው ወቅት ስለ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች በኬንያና በታንዛኒያ ሀገር አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የሚያጋጥማቸውን አደጋና እንግልት በጋራ ለመቅረፍ የሚያስችል ተግባር ለማከናወን ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአደገኛ እፅ ዝውውርን በጋራ ለመግታት፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ከታንዛኒያ ፖሊስ አካዳሚ ጋር በአቅም ግንባታ ላይ አብሮ ለመስራትና ከአንጋፋው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የተሻለ ልምድ እንዲሁም የታንዛኒያን ልምድ ለማካፈል ተስማምተዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ስራ በወንጀል መከላከል፣ በምርመራና በቴክኖሎጂ ተቋሙ የደረሰበት ደረጃ ለልዑካን ቡድኑ ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡
የታንዛኒያ ፖሊስ ልዑክ መሪ ኢንስፔክተር ጄነራል ሲሞን ኞኮሮ ስሮ በጉብኝቱ ወቅት ስለተመለከቱት የለውጥ ስራዎች ያላቸውን አድናቆት ገልፀው ፥ ለተደረገላቸው አቀባበልም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አንድ ቡድን ወደ ታንዛኒያ ሄዶ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለመመልከትና ከእስር አስፈትቶ ወደ አገራቸው ለማስመለስ የሚያስችል የመፍትሄ ሀሳብ በጋራ ለማፈላለግ ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም የሁለቱን ሀገራት የፖሊስ ግንኙነት ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ በታንዛኒያ በመፈራረም የተጀመረውን ፖሊሳዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሁለቱ ሀገራት ፖሊስ ኃላፊዎች መስማማታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።