Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ጉዳት ባደረሰባቸው የአማራ ክልል 8 ዞኖች የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ባደረሰባቸው የአማራ ክልል ስምንት ዞኖች የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራዎች እንደቀጠሉ መሆናቸው ተገልጿል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ስዩም መኮንን በሰጡት መግለጫ፥ በሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች 288 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማውደሙን አንስተዋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የሚከናወኑት የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ተግባራትም መቀጠላቸውን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ተግባሩ በሁለት መንገድ የሚከወን ሲሆን÷ የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ ዘላቂ እቅዶች በሚል ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።
በመልሶ ማቋቋም ስራው እንደ ጤና ትምህርትና ግብርና ያሉ ተቋማት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው አብዛኞቹ መጠነኛ አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ ደግሞ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ በማሟላት ፈጥነው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጦርነቱ በርካታ ጉዳቶችን ከማስከተሉ በተጨማሪ ሌሎች የውስጥ ችግሮችም እንዲበራከቱ መንገድ ከፍቷል ያሉት አቶ ስዩም፥ ህብረተሰቡ የውስጡን ሰላምና አንድነት በማስጠበቅ መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እስካሁን ሁለት ቢሊየን በሚጠጋ ገንዘብ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት እንደተከናወኑ ጠቁመው÷ የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑና በመንግሥት አቅም ብቻ የሚከወን ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም ልዩ ልዩ የሃብት ማሰባሰብ ተግባራትን በመከወን የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት እቅድ የተያዘ ሲሆን ÷ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍም የዚሁ ተግባር አካል እንደሚሆን ጠቁመዋል።
አሁን ላይም የሽብር ቡድኑ ለዳግም ወረራ እንደተዘጋጀ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች እየታዩ በመሆኑ ከመልሶ ግንባታ ጎን ለጎን ጠላትን የመመከት ዝግጅቶች እንደሚከወኑም አስገንዝበዋል።
በሙሉጌታ ደሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.