Fana: At a Speed of Life!

በ41 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የከረጢት ፋብሪካ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን አረርቲ ከተማ አስተዳደር በ41 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የከረጢት ፋብሪካ ተመረቀ፡፡
የከረጢት ፋብሪካው የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የተመረቀው፡፡
የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ሰናይ እማዩ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለ145 ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፥ በሰዓት 2 ሺህ 500 ሜትር ወይም 2 ሺህ ከረጢት የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ፋብሪካው ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግር ስላጋጠመው በሚጠበቅበት ልክ መስራት እንዳልቻለም ተናግረዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው የፋብሪካው መመረቅና ወደ ስራ መግባት የአካባቢውን ኢንቨስትመንት እንደሚያነቃቃዉ ገልጸው፥ የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ክልሉ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም በአረርቲ ከተማ አስተዳደር ስራ ጀምሮ ያቋረጠውን የሴራሚክ ፋብሪካ በሰኔ ወር ኃይል በማቅረብ ስራ ለማስጀመር ሂደት ላይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ፋብሪካው በ7 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ እና ግንባታውበ2008 ዓ.ም መጀመሩን ከምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ያገኘ ነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.