Fana: At a Speed of Life!

ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን ድባጢ ወረዳ የሕዝቦችን የቆየ የጋራ አብሮነት ለማጠናከር እና ግጭቶችን በይቅርታና በእርቅ በመፍታት ሂደት በተሰራው ስራ የተፈናቀሉ ወገኖችን የመመለስ ስራ ተጀመረ፡፡
የድባጢ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ዋውያ÷ በሳስ ማንደል ቀበሌ በነበረው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው በወረዳው ማዕከል የነበሩና እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ 411 ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሕግ ማስከበር ስራው ጎን ለጎን የሕዝቦችን አንድነት እና አብሮነት በማጠናከር ተፈናቃይ ወገኖችን ወደነበሩበት የመመለስ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል መባሉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና መልሶ ለማቋቋም የሚሰራውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ግብረ ኃይል የተቋቋመ ሲሆን፥ ለግብረ ኃይሉ አባላት የሥራ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
የሥራ አቅጣጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላና የአደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ልጃለም መሆናቸውን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.