ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተሰጠው የቴሌኮም ፈቃድ በምርጥ የሕዝብ አገልግሎት ምድብ አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ) ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተሰጠው የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ሂደት በእንግሊዙ የሽልማት ድርጅት የ2022 አሸናፊ ሆኖ ተመረጠ፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በተመራውና የቴሌኮም ዘርፍን ለውድድር ክፍት በማድረግ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተሰጠው አዲስ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ሂደት በምርጥ የሕዝብ አገልግሎት ፕሮጀክት ምድብ እንግሊዝ በሚገኘው የልማት አጋር ሽልማት ድርጅት አሸናፊ ሆኖ መመረጡ ተገልጿል፡፡
የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጡ ሂደት በፈረንጆቹ የ2022 አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው በኢነርጂ፣ በውሃና በቴሌኮም ዘርፍ ምድብ ሲሆን ሽልማቱም ለገንዘብ ሚኒስቴር ተበርክቷል፡፡
የሽልማት ድርጅቱ ዳኞች÷ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ የመስጠት ፕሮጀክት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማበረታታት፣ በስራ እድል ፈጠራ እና በቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መሻሻል ረገድ ለሀገር ልማት እና ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን ትልቅ ፋይዳ መገንዘባቸው ተገልጿል፡፡
ፈቃድ የመስጠት ሂደቱም÷ በጥንቃቄ እና ግልፅነትን በተላበሰ መልኩ የተመራ መሆኑ ፕሮጀክቱ እውቅናና ሽልማት እንዲያገኝ ያስቻሉት ቁልፍ መስፈርቶች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ሂደቱ በአሸናፊነት የተመረጠው÷ ከ5 የተለያዩ በአገልግሎት ዘርፍ በእጩነት ቀርበው ከነበሩ ፕሮጀክቶች መካከል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡