Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ እንዲሄድ የወሰደውን አዎንታዊ እርምጃ እናደንቃለን- የአውሮፓ ሕብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግይ ክልል እንዲሄድ የወሰደው አዎንታዊ እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን የአውሮፓ ሕብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺቺ ጋር ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው ወቅት ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ላላት አጋርነት ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸው÷ ከኮሚሽኑ እና ከአባል ሀገራቱ ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እየሠራች መሆኑን ተናግረዋል።
በግጭት ለተጎዱ ወገኖች እየተደረገ ካለው ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም÷ በትግራይ ክልል የሚደርሰው ዕርዳታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳምንት 500 የጭነት መኪኖች ከያዘው ግብ ባለፈ የማድረስ ደረጃ ላይ መድረሱን አስረድተዋል።
አጋር አካላት የአማራ እና አፋር ክልሎችን ጨምሮ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ እንዲያፋጥኑም ጠይቀዋል።
ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺቺ በበኩላቸው መንግስት በዚህ ረገድ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው፥ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያቀርቡ አጋሮች ተጨማሪ ነዳጅ፣ ጥሬ ገንዘብ እና ሌሎችም ድጋፎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት በተከሰቱት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የተጠያቂነት እርምጃ እንዲሁም ይህንን የሚያረጋግጥ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በማቋቋም እና በሰብአዊ መብት አያያዝ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ላይ ስላሉ ጉዳዮችም ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግስት እየወሰደ ስላለው እርምጃ እና ሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክር በሚመለከት ለኮሚሽነሩ ባደረጉት ገላጻ÷ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኩል እየተደረጉ ያሉ የሰላም ጥረቶች ላይ ያለውን ሁኔታ ማስረዳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሰላም ውጥኖች ላይ ህወሓት ያሳየውን ተገቢ ያልሆነ የመጠራጠር አቋምም አመላክተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.