Fana: At a Speed of Life!

ዴንማርክ በኢትዮጵያ በሥርዓተ ፆታና በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የሚከናወኑ ስራዎችን አግዛለሁ አለች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴንማርክ በኢትዮጵያ በስርዓተ ፆታና በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የሚከናወኑ ስራዎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ እስሚዝ ሲንደበርግ ጋር መክረዋል።

በውይይታቸውም አምባሳደሯ ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ግጭት እንዲቆምና በግጭቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ እንዲሁም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በማቋቋም በግጭቱ ምክንያት የተፈጸሙ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመመርመር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

በቀጣይም መንግሥታቸው የሥርዓተ ፆታን ጉዳይ በሁሉም መስኮች በማካተትና የሰብዓዊ ድጋፎችን በግጭቱ ምክንየያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እንዲደርስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ፥ በግጭቱ ምክንያት ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመመርመርና አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ በመንግሥት በኩል የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አብራርተው ፥ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴት የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርጉ የማህበራዊና ሥነ ልቡናዊ ድጋፎችን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የሚያጎለብቱ የገቢ ማስገኛ ዘርፎችን በአንድ ማዕከል የሚያገኙበትን አሰራር የመዘርጋት ስራን አጠናክሮ እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አምባሳደሯ በበኩላቸው ፥ ሀገራቸው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል የስርዓተ ፆታን የማካተትና የሰብዓዊ ድጋፎችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ለኢትዮጵያ እንዲደርስ እያደረጉ መሆናቸውንና በቀጣይም የሥርዓተ ፆታን በተመለከተ የሚተገበሩ ሀገራዊ ፕሮግራሞችን በቅንጅት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆኑ ነው የገለጹት፡፡

ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ፥ መስሪያቤታቸው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ በግጭቱ ምክንያት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች የማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የክህሎት ስልጠና ለመስጠት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንና በዚህ ረገድ ዴንማርክ ከችግሩ ስፋት አንጻር ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.