Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማገርሸቱን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ቀንሶ የነበረው የኮቪድ -19 ጽኑ ሕሙማን ቁጥር አሁን ላይ እየጨመረ እንደመጣና 70 ሰዎችም በጽኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቶ እንደነበርና ከባለፈው ወር ወዲህም ምንም አልጋ የያዙ ሕሙማን እንዳልነበሩ ጤና ሚኒስቴር አስታውሷል፡፡

አሁን ላይም በማኅበረሰቡ ዘንድ ከመዘናጋትም በላይ ቫይረሱ እንደጠፋ ተደርጎ እየተወሰደ እንደሚገኝም ሚኒስቴር አመላክቷል፡፡

ይህ በኅብረተሰቡ ላይ እየተስተዋለ የመጣው የመዘናጋትና ወረርሽኙን አቅልሎ የመመልከት ባሕሪ ወረርሽኙ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዳግም እንዲያገረሽ ማድረጉን ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔም አሁን ላይ በአማካይ ከ12 በመቶ በላይ መድረሱም ነው የተነገረው፡፡

በመሆኑም ተገቢውን ጥንቃቄ እና የመከላከል ሥራ መስራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ሕብረተሰቡ፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ማኅበራት ፣ የጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የመከላከያ መንገዶቹን ያለመሰላቸት ማስተማር፣ ማሳሰብ እና እራሳቸውም በመተግበር ዓርዓያ መሆን ይኖርባቸዋልም ተብሏል፡፡

ሚኒስቴሩ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታትና ለመከላከልም ሦስተኛ ዙር የኮቪድ19 ክትባት ዘመቻ ከሰኔ 2 ቀን 2014 ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ መስጠት መጀመሩም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ ሂደትም 22 ነጥብ 4 ሚሊየን የክትባት ዶዝ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

የመከላከያ ክትባቱ ÷ ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲሁም በጽኑ የመታመምና የመሞትን ዕድል ለመቀነስ ስለሚያስችል ዕድሜያቸው 12 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻው ወቅት ክትባቱን እንዲወስዱ ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡

ከዚህ በፊት የኮቪድ 19 በሽታ መከላከያ ክትባት 1ኛ ዶዝ ወስደው ሁለተኛውን ዶዝ ለመውስድ ጊዜያቸው የደረሰ ሰዎች ፣ እንዲሁም መከላከያ ክትባቱን ሙሉ ለሙሉ ወስደው ስድሥት ወር የሞላቸው ሰዎች የመከላከል አቅም የበለጠ የሚያሳድገውን የ“Booster dose” ክትባት እንዲከተቡ ጤና ሚኒስቴር ጥሪውን አቅርቧል፡፡

እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ486 ሺህ በላይ ሲሆን 7 ሺህ 530 ወገኖች ደግሞ ሕወታቸውን አጥተዋል፡፡

በዘቢብ ተክላይ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.