Fana: At a Speed of Life!

ወጣቶች አገር ለማፍረስ የሚሹ ኃይሎችን በጋራ በመመከት ለመጪው ትውልድ የበለጸገችና ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ማስረከብ ይኖርባቸዋል – ዶክተር ዓለሙ ስሜ

አዲ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቶች አገራቸውን እያለሙ አገር ለማፍረስ የሚሹ ኃይሎችን በጋራ በመመከት ለመጪው ትውልድ የበለጸገችና ሰላሟ የተረጋገጠች ሀገር ማስረከብ ይኖርባቸዋል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል እና በፓርቲው የሲቪክና ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ተናገሩ፡፡
ዶክተር ዓለሙ ስሜ በብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አስተባባሪነት በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን አራተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን አስጀምረዋል፡፡
በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለሀገር ግንባታ እና ለቀጣይ ትውልድ መሰረት የሚሆን ስራ ነው ብለዋል፡፡
የገጠመንን ፈተና እያሸነፍን ብልጽግናችንን እንደምናረጋግጥ ጥርጥር የለውም ያሉት ዶክተር ዓለሙ÷ ሰላም አልሻም በማለት ገፍቶ የሚመጣ ኃይል ካለ በሚገባው ቋንቋ አስረድተን እንመልሰዋለን ብለዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አስፋው ተክሌ በበኩላቸው÷ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ለነገዋ ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥል በመሆኑ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
በአራተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ወጣቶችን በማስተባበር 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች እንደሚተከሉም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ሌት ተቀን እየሰራች ባለችበት በዚህ ወቅት ጠላቶቿ አገርን ለማፍረስ ቢሰሩም÷ በወጣቶች ጥረት ማንም ኃይል ከብልጽግና ጉዟችን ሊያስቆመን አይችልም ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትራችን የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስኬታማነት÷ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ሚና አለው ማለታቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.