Fana: At a Speed of Life!

የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያን በማይተገብሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል – የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያን በማይተገብሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያ ቁጥር 908/2014 ከሐምሌ 5 ቀን 2014 ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም÷ ከስርጭት ትስስርና ከመሸጫ ዋጋ ጋር ተያይዞ ለተጠቃሚው እየደረሰ አለመሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በተደረገ ክትትልም÷ ሲሚንቶ ከተቀመጠው የስርጭት መመሪያ ውጪ ከፋብሪካዎች እየወጣ በተለያዩ መጋዘኖችና የሽያጭ ቦታዎች እንደሚገኝ መረጋገጡን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

በመሆኑም በየክልሉና ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከተው የፀጥታ ተቋም ጋር በመቀናጀትና የሲሚንቶ ግብይት ቁጥጥር ቡድን በማሰማራት÷ ከመመሪያ ውጪ እየተከናወነ የሚገኘውን ሕገ ወጥ የሲሚንቶ ግብይት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በአስቸኳይ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡

ተጠቃሚው የሲሚንቶ ምርት ማግኘት እንዲችል ለስርጭቱ የተመረጡ አካላት በአስቸኳይ ምርቱን ከፋብሪካ በመቀበል በተላለፈው ጊዜያዊ የመሸጫ ዋጋ እንዲያቀርቡ ሚኒስቴሩ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.