Fana: At a Speed of Life!

በ18ኛው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ያስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የጀግና አቀባበል ይደረግለታል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ያስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ዛሬም እንደ ትናንቱ፥ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን” በሚል መሪ ሀሳብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የውስጥ ፈተናውንና የውጪ ጫናውን ተቋቁመው በዓለም የስፖርት መድረክ ላይ በድል ላይ ድል የሚቀዳጁት፥ በስፖርት አደባባይ የእናት ሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ፣ ድል ባደረጉበት ሜዳ ላይ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው ፈጣሪያቸውን የሚያመስግኑ ኢትዮጵያውያን” መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በኦሪገን ያስመዘገበው አኩሪ ድል ከተባበርን በድል አድራጊነታችን እንደምንቀጥልና መሰናክሎችን ሁሉ እንደምንሻገራቸው ያሳየ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ናቸው።

አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ በፈፀሙት ጀግንነት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ እንዲልና ክብሯ እንዲወሳ አድርገዋል ሲሉም ነው የገለጹት።

በነገው ዕለት መንግሥት ለአትሌቲክስ ቡድን የጀግና አቀባበል እንደሚያደርግለት የገለጹት ዶክተር ቢቂላ፥  ኢትዮጵያ ታመስግን የሚል መርሐ ግብርም እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

በነገው ዕለት ሕዝቡ ለጅግኖች አትሌቶቹና ለሌሎች የልዑኩ አባላት አድናቆቱን በመግለጽ የጀግና አቀባበል የሚያደርግላቸው ሲሆን፥ የአትሌቲክስ ቡድኑ ካረፈበት ስካይላይት ሆቴል ከጠዋቱ  1፡00 ሰዓት ጀምሮ በአጀብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች በደማቅ ሁኔታ እንደሚጓዝ ታውቋል።

200 ሀገራት በተሳተፉበት 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተካፈለችው ኢትዮጵያ 4 የወርቅ ፣ 4 ብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን ከአፍሪካ በአንደኛነት ከዓለም ከአሜሪካ ቀጥላ በ2ኛ ደረጃነት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ነገ  የአትሌቲክስ ቡድኑ ካረፈበት ስካይላይት ሆቴል ጀምሮ  በአጀብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ስለሚጓዝ የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.