ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ምዝገባ ተራዘመ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ምዝገባ እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም መራዘሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ዜጎችን ሕጋዊ የማድረግ ምዝገባ እስከ ነሐሴ 13 ተራዝሟል ብለዋል።
እስካሁን በተደረገው ምዝገባ ከ70 ሺህ በላይ የሚሆኑ የ36 አገራት ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
ምዝገባው የተራዘመው በመጀመሪያ ዕድል ያልተመዘገቡ ሌላ ዕድል እንዲያገኙ በማሰብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አምባሰደር መለስ በመግለጫቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር በሰላም እንዲፈታ አሁንም ፅኑ አቋም መኖሩን አንስተዋል።
ችግሩን ለመፍታት የሰላም አማራጩ የሚካሄደው በአፍሪካ ሕብረት በኩል ብቻ እንደሆነና ሌላ አካል ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል።
ከሰሞኑ በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ኮሚሽን ወጣ የተባለ ሐሰተኛ መረጃ እንጂ ሕጋዊ ሰነድ እንዳልሆነ ጠቅሰው፥ በአፍሪካ ጉዳይ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ከአፍሪካ ሕብረት ጋር አቻ አድርጎ ማንሳትም ቅቡልነት እንደሌለው ገልጸዋል።