Fana: At a Speed of Life!

የሕዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቀቀ፡፡

የክረምት ወቅት መግባትን ተከትሎ ለሶስተኛ ጊዜ ሲካሄድ የቆየው የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት ውሃው በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ማብሰሪያው ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አሁን ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ስራዎች ግንባታ 95 በመቶ የደረሰ ሲሆን÷ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸምም 87 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱ ተመላክቷል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ስራ በትናንትናው ዕለት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በትናንትናው ዕለት ስራ የጀመረው ዩኒት ዘጠኝ ሲሆን፥ ባለፈው የካቲት ወር ዩኒት10 ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የሚታወቅ ነው።

ግድቡ አሁን ባለው ከፍታና በያዘው የውሃ መጠን ሁለቱ ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት ሃይል እያመነጩ ይገኛሉ።

ግድቡ በሙሉ አቅሙ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር ደግሞ እያንዳንዱ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ሃይል የሚያመነጭ ይሆናል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፥ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።

ግድቡ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ስፋት የሚሸፍን ሲሆን፥ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ መጠን ይይዛል።

በአልአዛር ታደለ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.