Fana: At a Speed of Life!

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር በኃላፊነት እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገር ግንባታና የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በኃላፊነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር ከቅን ልቦች በጎ ስራ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መድረክ “ማህበራዊ ሚዲያ ለሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኃላፊነት የጎደላቸውና በስሜት የሚነዱ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሚያሰራጯቸው የሀሰት መረጃዎች በተለያዩ ሀገራት ጉዳት ከማስከተላቸው ባለፈ፥ ሀገራትን እስከ መፍረስ ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም በማህበራዊ ሚዲያ ልዩነትን የሚሰብኩ ሀገርን እና ሰላምን የሚያደፈርሱ መረጃዎች ሲሰራጩ እንደሚስተዋል ነው የተናገሩት፡፡

ማህበራዊ ሚዲያው በአግባቡ ከተጠቀሙበት ከውድቀት የሚታደግ፣ ሰላም እና ልማትን የሚያረጋግጥ፥ አንድነትን የሚሰብክ፣ ሌብነትን የሚቃወም ትውልድ የሚያፈራም ይሆናል ነው ያሉት።

በአዳነች አበበ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.