ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አልጀርስ የሚገኘውን የሰማዓታት መታሰቢያ ሙዚየም ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአልጀሪያ እያደረጉት ባለው ይፋዊ የስራ ጉብኝት በርዕሰ መዲናዋ አልጀርስ የሚገኘውን የሰማዓታት መታሰቢያ ሙዚየም ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው የአበባ ጉንጉንም አኑረዋል።
በአልጀርስ የሚገኘው የሰማዕታት መታሰቢያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1982 አልጀሪያ 20ኛ ዓመት የነጻነት በዓሏን ስታከብር ለአገሪቷ ነጻነት የህይወት መሰዋዕትነት የከፈሉ ዜጎችን ለማሰብ ነው በይፋ ተመርቆ ለጎብኝዎች ክፍት የሆነው።
የሰማዕታት መታሰቢያው በውስጡ 302 ጫማ ርዝመት ያለው ሐውልትና አልጀሪያውያን ለአገራቸው ነጻነት የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ ሙዚየም ይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትናነትናው እለት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አልጀሪያ መግባታቸው ይታወሳል።
በቆይታቸውም ከአልጀሪያ ፕሬዚዳንት አብዱል መጅድ ታቡኔ ጋር በመገናኘት የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያና አልጀሪያ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነት ቢኖራቸውም፥ ግንኙነታቸውን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ያህል እንዳልሰሩ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋዊ የስራ ጉብኝትም የዚሁ ማሳያ ነው።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!