Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ያለው ጽኑ አቋም የሚደገፍ መሆኑን እስራኤል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ያለው ጽኑ አቋም የሚደገፍ መሆኑን በእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ኮሎኔል አቪዜር ሴጋል ተናገሩ፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ ከእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ከሆኑት ኮለኔል አቪዜር ሴጋል እና ረዳታቸው ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ÷ አምባሳደር ረታ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በመንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱን አብራርዋል።

ይህን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት እየወሰደ ያለውን የሕዝብን ደህንነት የማስከበር እርምጃ በዝርዝር በማስረዳት የመንግሥትን አቋም አስረድተዋል።

አምባሳደር ረታ ይህን ሁኔታ የእስራኤል መንግሥት አካላት እንዲረዱና የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ሂደቱ እንዲቀጥል ለሚያደርገው ጥረት ድጋፍ እንዲያደርጉ እንዲሁም የሽብር ቡድኑን ተግባር እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

ታሪካዊ የሆነው የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት በወታደራዊ መስክ ይበልጥ እንዲጠናከር በመንግሥት በኩል ፍላጎት መኖሩንና በጋራ ለመስራትም ዝግጁነት እንዳለ አስታውቀዋል።

የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ኮለኔል አቪዜር በበኩላቸው ÷ጉዳዩን እየተከታተሉት እንደሆነ ጠቁመው የኢትዮጵያ መንግሥት ለሠላም ያለው ጽኑ አቋም የሚደገፍ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የአገር ሉዓላዊነትን ማስጠበቅና የሕዝብን ደህንነት የማስከበር ተግባር እንደሚረዱም አስታውቀዋል።

ህወሓት ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት መጀመሩ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ የከፈተው ጦርነትና የሽብር ድርጊት በየትኛውም መንገድ የሚወገዝ መሆኑንም መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ ለእስራኤል በአፍሪካ በጣም አስፈላጊ ወዳጅ አገር መሆኗን እና በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ያለው ወታደራዊ ትብብር ጠንካራ እና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.