ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው – ኢንጂነር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ የሚገቡ ከማዕድን የሚሰሩ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ከዚህ ቀደም ለማዕድን የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን ኢትዮጵያ ከዘርፉ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም እንዳታገኝ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ሀገሪቱ እስካሁን ከማዕድን የሚሰሩ ግብዓቶችን በውድ ዋጋ እና ምንዛሬ ከውጭ ሀገራት እንደምታስገባ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይም በዘርፉ ሀገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍሉ ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ አብዛኛዎቹ ስራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ በ2015 በጀት ዓመት ምርቱን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዓመት 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ መተከሉን አንስተዋል፡፡
በተመሳሳይ የእብነ በረድ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከፍተኛ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ አሁን ላይ የመቁረጥ እና የማስዋብ ስራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡
የሴራሚክ ምርትን ከሰባት ወራት በኋላ ከውጭ የማስገባቱ ሒደት እንዲቆም የሚያስችል ደረጃ ላይ መደረሱንም አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ የዘለቀውን የብር ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በዋና እቅድነት ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል፡፡
በዚህ መሰረት የብረት ክምችት ያለባቸውን ቦታዎች የመለየቱ ስራ መከናወኑን እና የአዋጭነት ጥናት እና የአማካሪ ድርጅቶችን የመቅጠር ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውጭ ምንዛሬ የሚገባውን አፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለመተካትም 98 በመቶ በግብዓትነት የሚያገለግለውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡