Fana: At a Speed of Life!

የደመራ እና ኢሬቻ በዓላት እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና የወጣቶች ሚና ዙሪያ ከከተማዋ ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ተወያዩ።
 
የውይይቱ አላማ ወጣቶች በወቅታዊ ሁኔታ ላይ በቂ ግንዛቤ አዳብረው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግና በተለይም ከፊታችን የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ማስቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
ወጣቶቹም በውይይቱ በዓሉ በሰላምና በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
 
በየደረጃው አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግም ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር አንድነትን እና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊያከብሩ መዘጋጀታቸውንም ነው የገለፁት።
 
በዚሁ መድረክ ማጠቃለያ ላይ አስተያታቸውን የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ “በግንባር የከሰረው የሽብር ቡድን በአደባባይ የሚከበሩ ህዝባዊ በዓላትን የመጠቀም ፍላጎት እንዳለው ከአንዳንድ ፍንጮች ለመረዳት ተችሏል” ብለዋል።
 
በመሆኑም በአደባባይ የሚከበሩ ሕዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት ትውፊታቸውንና ኃይማኖታዊ እሴታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ነው ያሳሰቡት።
 
ከንቲባ አዳነች ከወጣቶች ጋር በዘላቂነት እየተነጋገሩ ችግሮችን እየፈቱ ለመሄድ ከተማ አስተዳደሩ ዘውትር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል ።
 
ባለፉት ግዜያት ከወጣቶች ተጠቃሚነት አንጻር ሰፊ ክፍተት መኖሩ በአሀዝም ጭምር የተረጋገጠ ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ ከለውጡ ወዲህ ከተማ አስተዳደሩ ጸጋዎችን በመለየት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ይህም ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል ።
 
በመተባበር ፣ በመስከንና ስንፍናን በማስወገድ ያሉ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም ብሎም ለችግሮች ያለመንበርከክ አቅምን በማዳበር ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ከንቲባ አዳነች መናገራቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.