ሚኒስቴሩ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እየሰራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የኃይል መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ሚኒስትሩ ዶ/ር አንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት ፥ የመልሶ ግንባታ ሥራው የሚካሄደው ለዞንና በርካታ ቁጥር ላላቸው ከተሞች ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ነው።
አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ የያዘውን ግብ ለማሳካት አጎራባች በሆኑት አማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን አስታውሰዋል።
የሽብር ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎች የህዝብ መገልገያ የሆኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የኃይል መሰረተልማቶችን ከመዝረፍ ባለፈ አውድሟል።
“ይህም በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመ አንዱ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ፥ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ግብ ተይዞ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመልሶ ግንባታ ሥራው የውሃ መስመሮችና ጀነሬተሮችን ጨምሮ ሌሎች የወደሙና የተዘረፉ ቁሶችን መተካት ላይ አተኩሮ እንደሚከናወንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት የመልሶ ግንባታ ሥራው በተወሰነ ደረጃ መካሄዱን አስታውሰው ፥ ዘንድሮ የመልሶ ግንባታ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ችግሩ ያልተፈታባቸው የዞን ከተሞችን በማስቀደም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
“ለዚህም እንደ ዩኒሴኤፍ ካሉ ግብረ ሰናይ ደርጅቶች የተገኙ ጀነሬተሮችን በማከፋፈል ከአጭር ጊዜ አኳያ ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል” ብለዋል።
የደበብ ክልል ውሃ፣ ኢነርጂና ማዕድን ሃብት ቢሮ ምክትል የኃላፊ ኢንጂነር ፍጹም መኩሪያ በበኩላቸው፥ “በጦርነቱ የአማራና አፋር ክልሎች በዋናነት ሰለባ ቢሆኑም ጉዳቱ ለአገር የተከፈለ ዋጋ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም” ብለዋል።
በእነዚህ ክልሎች የደረሰውን ውድመት መልሶ በመገንባት ረገድ ሁሉም ክልሎች የየራሳቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
“በክልሉቹ በንጹህ መጠጥ ውሃም ሆነ በኢነርጂ ዘርፎች የወደሙ የሀገር ሀብቶችን በመተካት የማገዝ ሚናችን እንወጣለን” ሲሉም ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት የተለየ የድጋፍ ስትራቴጂ በመቀየስና በእነሱ አቅም ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊገነቡ የሚችሉትን ለይቶ በመገንባት ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚመቻችም አመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!