Fana: At a Speed of Life!

መንግስትና ሕዝብ የታወጀባቸውን ጦርነት በመመከት የልማት ሥራ እየሠሩ ፈተናን መቋቋም እንደሚቻል አሳይተዋል – አቶ ንጉሡ ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስትና ሕዝብ የታወጀባቸውን ጦርነት በመመከት የልማት ሥራ እየሠሩ ፈተናን መቋቋም እንደሚቻል አሳይተዋል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገለጹ፡፡

የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስተዋወቂያ ውይይት በባህርዳር ከተማ አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ ንጉሡ ጥላሁን÷የአማራ ክልል እንደ ክልል፣ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የታወጀባቸውን ጦርነት በመመከት የልማት ሥራ እየሠሩ ፈተናን መቋቋም እንደሚቻል አሳይተዋል ብለዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ከስልጠና በላይ በሥራ ዕድል ፈጠራ ከዳቦ መብላት ባሻገር የሀገር ውስጥ ምርትን በመጨመር ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች መቀነስ እና የውጭ ገበያን ማሳደግ ፥ መሠረታዊ ፍላጎትን ከማሟላት በላይ ሀብት የሚፈጥሩ ዜጎችን በማፍራት የዋጋ ንረትን መቀነስ ኃላፊነት እንደተሰጠው ነው የገለጹት።

ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ እና የሀገር ብልፅግና ዕውን እንዲሆንም ትልቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ነው ያሉት አቶ ንጉሡ።

በያዝነው ዓመትም ለ3.7 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የማመቻቸት ዕቅዱን ከክልሎች ጋር ተባብሮ ለማሳካት መግባባት ላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

ክልሉ የወደሙ ተቋማትን መልሶ እየገነባ እና ጀግኖችን እያበረታ በበጀት ዓመቱ ከ900 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማመቻቸቱ ችግርና ፈተናን ተቋቁሞ ሥራን መሥራት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የገለጹት አቶ ንጉሡ÷ ባለፈው ዓመት ሚኒስቴሩ ተቋሙን እያደራጀ የተሰጠውን ተልዕኮ በመወጣት ስኬታማ ሥራ እንዳከናወነ አንስተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሽልማት መበርከቱን ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.