አርሶአደሩ የመስኖ ግድቦችን በስፋት መጠቀም አለበት – ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየአካባቢው ያለ አርሶአደር ትንንሽ ግድቦች እና በቀጣይ ወደሥራ የሚገቡትን ትላልቅ ግድቦች በመጠቀም በመስኖ ልማት ላይ በስፋት መሳተፍ እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡
አርሶ አደሮች የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማትን ከድህነት መውጫ መንገድ ሊያደርጉት እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2015 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ እና ሌሎች የፌደራልና የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዘርፉ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በበጋ መስኖ ስንዴ የተሠራው ሥራ ብዙ ተስፋዎች ታይቶበታል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር ለበጋ መስኖ የተመቸ ቢሆንም እስካሁን በሚፈለገው ልክ ማልማት አለመቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት 80 ሺህ ሔክታር በበጋ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ÷ 40 ሺህ ሔክታር በበጋ የመስኖ ስንዴ ማልማት መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ሀገራችን በጦርነት ላይ ሆና ሁሉም ነገር ወደ ግንባር በተባለበት ወቅት የዕቅዱ 50 በመቶ መሸፈኑ ትልቅ ስኬት ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል፡፡
ለዚህም የግብርና ሚኒስቴር፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና አመራሮች እና ባለሙያዎች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባል ነው ያሉት፡፡
ግብርናውን በማዘመን እና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡን ከድህነት ለማላቀቅ ሁሉም የራሱን ዕቅድ በመያዝ በዚህ ዓመት በተለየ ትኩረት እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡
ታታሪው አርሶ አደር ቴክኖሎጂ እና በየአካባቢው የሚገኙ ውኃን በአግባቡ በመጠቀም በዚህ ዓመት ለውጥ በማምጣት ድህነትን ማስወገድ ትችላላችሁ፤ ለዚህም መንግሥት የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው እንደገለጹት÷ በተያዘው ዓመት 250 ሺህ ሔክታር በበጋ የመስኖ ስንዴ ለመሸፈን ዕቅድ ተይዟል፡፡
በተያዘው ዓመት የስንዴ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙም ተገልጿል፡፡
በምንይችል አዘዘው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!