Fana: At a Speed of Life!

በአሶሳ ከተማ ሲከበር የቆየው የቱሪዝም ቀን ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣መስከረም 15፣2015(ኤፍ ቢሲ) “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአሶሳ ከተማ ሲከበር የቆየው የቱሪዝም ቀን ተጠናቀቀ፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በአገራችን የተከበረው የቱሪዝም ቀን ትውልዱ እራሱን እና ሀገሩን ለቀሪው ዓለም እንዲያስተዋውቅ እድል የፈጠረ ነው፡፡

የተጀመረው የሀገር ውስጥ የቱሪዝም ንቅናቄ፥ የሀገርን ገፅታ በመገንባት የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን የመጎብኘት ልምዱን በማስፋት በዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚያገለግል ነው ያስታወቁት፡፡

የሚቀጥለውን ዓመት የዓለም የቱሪዝም ቀን ለማዘጋጀት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተመረጠ ሲሆን፥ ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ ሁነቱ ያግዘዋል ተብሏል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ሁነቱ በሰላም በመጠናቀቁ ለከተማው ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

ክልሉ እምቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉት፥ በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀጣይ በቱሪስቶች በስፋት ተመራጭ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት በቱሪስት መዳረሻዎችና እና በከተማ ልማት ላይ በስፋት እንደሚሰራም  ርዕሰ መስተዳደሩ  አመላክተዋል።

በሜሮን ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.