Fana: At a Speed of Life!

በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ያተኮረ ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ያተኮረ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለፁ።

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኤሌክትሪክ ላይ የተመሰረተና “ጤናማ ትራንስፖርትን ማበረታታት” በሚል መሪ ሃሳብ ምክክር እየተካሄደ ነው።

ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለፁት÷ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዓለም ላይ ከፍተኛ የድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅና ሌሎች ችግሮች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ በነዳጅ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

በቀጣይ 10 ዓመት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችንና የህዝብ ትራንስፖርቶች ወደ አገልግሎት ለማስገባት የማበረታቻ ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲም በኤሌክትሪክ የሚሰራ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ካሪኩለም ቀርፆ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የሰለጠነና የበቃ የሰው ሃይል ለማቅረብ በጥናት ላይ ተመስርቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሪክ መኪኖች የሚገጣጥሙ ድርጅቶች ያላቸው ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የፌዴራል የስራ ሀላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.