Fana: At a Speed of Life!

በታሪክ፣ በቅርስ ጥበቃና በአርኪዮሎጂ ሥራዎች የፈረንሳይ አጋርነት ዘመናትን የተሻገረ ነው – ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ መስከረ ም 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በታሪክ፣ በቅርስ ጥበቃና በአርኪዮሎጂ ሥራዎች ላይ የፈረንሳይ አጋርነት ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በአዲስ መልክ ያደራጀው የብሔራዊ ሙዚየም የአርኪዮሎጂ ዐውደ ርዕይ በይፋ ተመርቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ በታሪክ፣ በቅርስ ጥበቃና በአርኪዮሎጂ ሥራዎች ላይ የፈረንሳይ አጋርነት ዘመናትን የተሻገረ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ የተገኙ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች በሁለቱ ሀገራት ባለሙያዎች ዕውን የሆኑ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በብሔራዊ ሙዚየም ይፋ የሆነው የአርኪዮሎጂ ዐውደርዕይ ፥ ለሕዝብ ዕይታ ያልቀረቡ ቅርሶችን ከመያዙም በላይ ከዚህ ቀደም ያልተካተቱ እንዲካተቱ መደረጉን አድንቀዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው ÷ ጥንታዊ ቅርሶቹ በተደራጀና በሣይንሳዊ መንገድ ባለመቀመጣቸው ለጎብኝው ምቹ እንዳልነበሩ ጠቅሰዋል፡፡

በፈረንሳይ ኤምባሲ ድጋፍ አሁን የተደራጀው ዐውደ ርዕይ ግን በዘርፉ የነበሩ ችግሮችን ይቀርፋል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት ሊገልፅ የሚችል ሙዚየም ለመገንባት መታሰቡንም ነው የጠቆሙት፡፡

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚይ ማሪሽ ÷ በቅርስ ጥበቃ፣ በታሪክና አርኪዮሎጂ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመሰል ሥራዎች ላይ ይሄው ተባብሮ መሥራት እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡

በሙዚየሙ በመካከለኛው ዘመን የነበሩ በአርኪዮሎጂ ግኝት የተገኙ እስላማዊ ቅርሶች መካተታቸውም ተገልጿል፡፡

በወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.