Fana: At a Speed of Life!

የኢሬቻ በዓል አስደናቂ በሆነ መልኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እናመሰግናለን – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል አስደናቂ በሆነ መልኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ በክልሉ ሕዝብና መንግሥት ስም አመሰግናለሁ ሲሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

የኢሬቻ በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን አስመልክቶ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት÷ መላው ሕዝባችን በተለይም የፀጥታ ኃይል አካላት በዓሉ እንዲሳካ ላደረጉት አስየዋጽኦ ምስጋናዬንና አድናቆቴን እገልጻለሁ ብለዋል።

የሚዲያ ተቋማት ስለበዓሉ ፋይዳ በመግለጽና የበዓሉን እሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ ለተጫወቱት አይተኬ ሚናም ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግናዋል።

ጠላቶቻችን እንደፈለጉትና እንደተመኙት ሳይሆን የኢሬቻ በዓል ከምንጊዜውም በላቀና በደመቀ መልኩ በሰላም ለመጠናቀቅ ችሏል ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ትናንት የተከበረው ሆረ ፊንፊኔ እና ዛሬ የተከበረው የሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓል 10 ሚሊየን ህዝብ ወጥቶ በዓላቱ አስደናቂ በሆነ መንገድ ሊከበሩ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይህም የህዝቡና የፀጥታ ኃይሉ እንዲሁም የተለያዩ መዋቅሮች የተቀናጀ የአመራር ብቃት ውጤት መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያመላከቱት።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ መግለጫቸው፥ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የጠላት ተልዕኮዎች ቢኖሩም የሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀረሰዴ የኢሬቻ በዓላት ምንም ዓይነት የፀጥታ ቸግር ሳይፈጠር በሰላም መጠናቀቃቸውን ነው የተናገሩት።

እነዚህ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የሀገሪቱ የፀጥታ መዋቅሮች ዘመናዊ የመረጃ ስልቶችን በመጠቀም በተደራጀ መንገድ ባደረጉት የመረጃ ልውውጥ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡

ይህም የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሳየ ተግባር በበዓሉ ላይ መታየቱን ነው ያመላከቱት፡፡

በመሰቀል በዓል ላይ የነበረው ሰለማዊ የበዓል አከባበር በኢሬቻም ተደግሟል ያሉት አቶ ሽመልስ፣ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስተዋፅኦ ላደረጉት ለሁሉም አካላት ምስጋና አቅረበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሁሉም ባህሎችና ወጎች ድምር ውጤት መሆኗን ያነሱት አቶ ሽመልስ፥ የአሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሽፋን ለሰጡ ሚዲያዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍ ብላ እንድትታይ ሁሉም ባህሎች በእኩልነት ሊስተናገዱ እንደሚገባ እና በቀጣይም ሀገራዊ እሴቶች በእኩልነት እንዲከበሩ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያን የሚመጥናት እና በታሪኳ ልክ ከፍ የሚያደርጋት የአንድነት እና የኅብረት ጉዞ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የሕዝብን አንድነት ለመጠበቅ ደግሞ የሕዝቦችን ባህል እና መገለጫዎች ማሳደግ የግድ አስፈለሳጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ኢሬቻን በቀጣይም ከፍ አድርጎ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያከብሩት በዓል እንዲሆን የሚያስችል ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.