Fana: At a Speed of Life!

ባንኩ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ውሳኔዎችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የተለያያዩ ውሳኔዎችን ይፋ አድርጓል፡፡

የባንኩ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ 391 የሚደርሱ በህገወጥ የገንዘብ ማዘዋወር ወይም ሀዋላ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው መዘጋቱን ተናግረዋል።

ተባባሪ የባንክ የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞችም እየተጣራ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ጠቅሰው÷ ሕገወጦችን ለሚጠቁሙ የህብረተሰብ ክፍሎችም የዎሮታ ክፍያ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

በባንክ ከተፈቀደው በላይ የገንዘብ መጠን የሚይዙትን ለጠቆሙ የተያዘው ገንዘብ 15 በመቶ፣ የውጭ ሀገር ገንዘብ ዝውውር ለሚጠቁሙ 15 በመቶ፣ ሕገወጥ ሀዋላን ለሚጠቁሙ 25 ሺህ ብር ዎሮታ እንደሚከፈላቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የወርቅ ኮንትሮባንድ ለሚጠቁሙ 15 በመቶ የወርቁን ዋጋ፣ የሀሰተኛ ኖት ህትመት ለሚጠቁሙ ከ20 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር እንደሚከፈልም ነው የተናገሩት።

በፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ እቃ የሚያስመጡ በውጭ ሀገር ያላቸውን የዶላር መጠን የሚያሳውቅ የባንክ ስቴትመንት ለብሄራዊ ባንክ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋልም ነው የተባለው።

ይህም ከሀገር ውስጥ ጥቁር ገበያ የውጭ ሀገር ገንዘብ በመግዛት ከውጭ እቃ እያስገቡ መሆኑ በመታወቁ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተወሰኑ ከውጭ በዶላር የሚገቡ የሸቀጥ አይነቶች ላይ ክልከላ ሊደረግ መሆኑን ዶክተር ይናገር ደሴ ገልጸዋል፡፡

በትእግስት አብርሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.