Fana: At a Speed of Life!

የአርብቶአደሮች ልማት ፎረም ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ልማት ፎረም ዛሬ ተመሰረተ፡፡

የፎረሙ መመስረት ዓላማም የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮችን የእንስሳትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት በማድረግ፣ የልማት አጋሮችን አቅም በማሰባሰብ በገበያ መር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ማስቻል ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማስፋት፣ አካታች የፋይናንስ አገልግሎትን በማጠናከር፣ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻልና አዲስ በመቅረጽ የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ከፍ ማድረግና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን እንደገለጹት÷ ሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሆነውን የእንስሳት ሀብት ልማት በአግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል በአስር ዓመቱ የግብርና መሪ ዕቅድ ውስጥ በማካተት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህ ፎረም በቀጣይ ያሉትን የእንስሳት ሀብትን ምርታማ ለማድረግ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን የፋይናንስ አቅርቦቱን በማመቻቸትና ህብረተሰቡን በማደራጀት የበኩሉን ሚና በመጫወት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ÷ አርብቶአደር አካባቢ በርካታ የእንስሳት ሀብት ያለው በመሆኑ ይህንን ሀብት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም አጋር አካላት በማስተባበር መጠቀም ከተቻለ በሀገር ደረጃ የተያዘውን ምርታማነት ማሳካት ይቻላል ብለዋል፡፡

ፎረሙ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አርብቶ አደር አካባቢዎችን ያካትታል መባሉን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.