Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ ሰራዊት ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀ የፎቶ ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ነገ የሚከበረውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀንን አስመልክቶ የተለያዩ ሁነቶች እየተካሄዱ ነው፡፡

በዛሬው ዕለትም “የጥንካሬያችን ምንጭ ህዝባችን ነው” በሚል መሪ ቃል የሰራዊቱን ቀን በማስመልከት የተዘጋጀው የፎቶ ዐውደ ርዕይ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡

ዐውደ ርዕዩን የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች መርቀው ከፍተዋል፡፡

ሚኒስትሩ የፎቶ ዐውደ ርዕዩ ታሪክን ጠብቆ ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ በመሆኑ ሌሎች የሰራዊቱንም ሆነ የተቋሙን የረጅም ዓመታት ታሪክ የሚያስመለክት ሙዝዬም እንደሚገነባ ተናግረዋል፡፡

ሙዝዬሙ እውን ለማድረግ በአዋጅ የተደገፈ ህግ መዘጋጀቱን ነው ዶክተር አብርሃም የገለጹት፡፡

ሙዝየሙ ለታሪክ አጥኚዎች፣ ለተመራማሪ፣ ለጸሃፊያንን እና መሰል ሙያተኞች ሰፊ ጥቅም ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዐውደ ርዕዩ የመከላከያ ሰራዊትን ከምስረታው እስከ አሁን ያለውን ሒደት የሚያሳይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

መርሐ ግብሩ ከ1900 እስከ 2015 ዓመተ ምህረት ማለትም ከፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ እስከ ዶክተር አብርሃም በላይ እንዲሁም ከሜጀር ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ እስከ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሚያስቃኝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ዓውደ ርዕዩ ከጥቅምት 15 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

ከሰዓታት በኋላም የመከላከያ ሰራዊት ቀንን አስመልክቶ የፓናል ውይይት የሚካሄድ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በኅይለየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.