Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስንዴ ምርትን ማገበያየት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተያዘው ዓመት የስንዴ ምርትን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ለማገበያየት መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የስንዴ ምርትን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ለማገበያየት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የስንዴ ምርትን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መምራት የሚያስችል ዝግጅት የተደረገ በመሆኑ በተያዘው ዓመት ማገበያየት እንደሚጀምር ነው ሥራሰኪያጇ የገለጹት፡፡

ምርት ገበያው ስንዴን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ማገበያየት የሚያስችለውን ረቂቅ ውል ያዘጋጀ ሲሆን ውሉን በማፅደቅ በዚህ ዓመት ማገበያየት እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

ምርት ገበያው ባሉት 25 ቅርንጫፎች አብዛኞቹ ከፍተኛ ስንዴ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ በመሆኑ አርሶ አደሩና አቅራቢው በቀላሉ ምርቱን ማስረከብ እንደሚችልም ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም አርሶ አደሩና አቅራቢው ምርቱን ወደ ምርት ገበያ ሲያመጣ ተፈትሾ ደረጃ ከተሰጠው በኋላ የአጭር ጊዜ ብድር ማግኘት የሚያስችለውን የመጋዘን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ሥርዓት መዘርጋቱም ተጠቁሟል።

በተመሳሳይም ምርት ገበያው የእጣን፣ ኮረሪማ፣ ሩዝና የግብጦ ምርቶችን በዚህ ዓመት ማገበያየት ይጀምራል ነው የተባለው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.