Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል መሬት ወስደው ባላለሙ ባለሀብቶች እና ፕሮጀክቶችን በሚያጓትቱ ተቋራጮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል መሬት ወስደው ባላለሙ ባለሃብቶች እና ፕሮጀክቶችን በወቅቱ በማያጠናቅቁ ተቋራጮች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

አቶ ኦርዲን በድሪ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን እና የጁገል ቅርስን ከአደጋ ለመጠበቅ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ጎብኝተዋል።

የጁገል ቅርስን ከአደጋ ለመጠበቅ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል።

አቶ ኦርዲን በድሪ በጉብኝቱ ወቅት÷ በክልሉ እየተጠናቀቁ የሚገኙ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ሁሉ አንዳንድ የዘገዩ የልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በጉብኝቱ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ለዘገዩ ፕሮጀክቶችም የተቋራጮች የአቅም ማነስና ለስራው ትኩረት ያለመስጠት ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስትም ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶችን ማበረታታት፣ መጠበቅና የሕግ ከለላ መስጠት ስራ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ለረዥም አመታት መሬት አጥረው በተቀመጡና መሬቱን ላልተገባ አላማ የሚያውሉ ባለሃብቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

የህዝብን ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት አንፃር ዳተኝነት በሚያሳዩ አመራሮች ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ስራም በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

የጁገል ቅርስን ከመጠበቅና ከመንከባከብ አኳያ ህዝቡ በባለቤትነት መንፈስ እያደረገ የሚገኘውን እንቅስቃሴ እና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.