Fana: At a Speed of Life!

የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን እንዲተገብር ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር ራሱን እንዲጠብቅ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

የወባ በሽታን ለመከላከልም÷ አጎበር መጠቀም፣ የመኖሪያ ስፍራዎችን ንጽህና መጠበቅ እና የጸረ ወባ ኬሚካል ማስረጨት ይገባል ነው የተባለው፡፡

በጤና ሚኒስቴር የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ቡድን መሪ ጉዲሳ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ በተለያዩ አካባቢዎች በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ በተካሔዱ ተግባራት ስርጭቱን ለመቀነስ ተችሎ እንደነበረ አስታውሰው÷ አሁን ላይ ግን እንደገና የማገርሽት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በ2015 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በአጠቃላይ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች ምርመራ አድርገው÷ 648 ሺህ 127 ሰዎች ላይ የወባ በሽታ እንደተገኘባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የበሽታው ስርጭት በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝች ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ መታየቱን ነው የተናገሩት፡፡

ወቅቱ ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ የሚከሰትበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን እዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይም ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች በመኝታ ሰዓት አጎበርን በመጠቀም በወረርሽኙ ከመያዝ ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ የሚል ስሜት፣ ራስ ምታት፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ህመም፣ የመገጣጠሚያ ህመም፣ ድካም፣ የልብ ምት መፍጠን፣ ምቾት ማጣት እና ሳል ሲከሰት የወባ በሽታ ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ወደ ጤና ጣቢያ በመሄድ እና ምርመራ እንዲያደርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.