Fana: At a Speed of Life!

ፈጣን፣ ጥራት ያለው እና ፍትሐዊ አገልግሎትን ማግኘት የዜጎች መብት ነው- የኦሮሚያ ክልል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈጣን፣ ጥራት ያለው እና ፍትሐዊ አገልግሎትን ማግኘት የዜጎች መብት ነው ሲል የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በመግለጫው በአንድ አገር ውስጥ በህዝብ ፈቃድ ስልጣን የያዘው መንግስት ለፖለቲካ ኢኮኖሚ ዕድገትና የማህበረሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለዜጎች ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት የመንግስት ግዴታ እንጂ እንደ ስጦታ የሚቆጠር ጉዳይ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ አገልግሎትን ለማግኘት የሚያስችለው አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ ከተገኘ በየደረጃው ካሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚፈልገውን አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው ተገልጿል፡፡

የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚጠበቅበትን መስፈርት አሟልቶ ለመጣ ባላጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባለው ደንብ፣ መመሪያ እና አዋጅ መሰረት ግልጽ እና ፍትሐዊ አግልገሎት የማግኘት መብት እንዳለው የታወቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት  እና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

በተለይም የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋት፣ አገሪቱ ያላትን መልካም እድል በመለየት ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ሁሉንም የአገሪቱ ዜጎችን በእኩልነት የሚታስተናግድ አገርን መገንባት፣ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እና የአገሪቱ ህዝቦችን ትስስር የሚያጠናክሩ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክቷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥ ከፍተኛ  ችግር እንዳለ መንግስት ሰፊ ጥናት በማድረግ አረጋግጧል ተብሏል በመግለጫው፡፡

በጥናቱ መሰረት በየደረጃው ባሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት ግልጽነት፣ ፍትሐዊነት እና ጥራት የሌለው፣ ባለጉዳዮችን የሚያመላልስ፣ የዜጎችን አገልግሎት ማግኘት መብትን ያልተገነዘበ፣ በሌብነት የተሞላ እና በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ ነው፡፡

እነዚህ ችግሮች በሁሉም የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚታዩ ቢሆኑም፣ ባለጉዳዮች በሚበዙባቸው መስሪያ ቤቶች ውስጥ ችግሩ በስፋት እንደሚስተዋል ተገልጿል፡፡

በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የደላሎች እጅ መግባት ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ነው የተገለጸው፡፡

ይህ ጉዳይ በመንግስት እና በህዝብ ግንኙነት ላይ ችግር የሚፈጥር፣ የብልጽግና ጉዞ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ እና ህዝቡን የሚያስከፋ ጉዳይ በመሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አቅጣጫ መቀመጡ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ህብረተሰቡ አገልግሎትን ፈልጎ ወደ መንግስት መስሪያ ቤቶች ሲሄድ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ መብቱን ለማስከበር ጎን ለጎን የህዝቡን ፍትሕ የሚያጎድሉ አካላትን በማጋለጥ ድጋፍ እንዲያደርግ የክልሉ መንግስት ጠይቋል፡፡

በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ግልጽነት እንዲኖረው እና በሚሰጠው አገልገሎት ተገልጋዩ እንዲረካ የአገሪቱ ሚዲያዎች የህዝቡን ዓይንና ጆሮ ሆነው ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.