Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካውያን ለኢንዱስትሪ ልማትና የእርስ በርስ ንግድ መጠናከር ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያን ለኢንዱስትሪ ልማትና የእርስ በርስ ንግድ መጠናከር ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ በኒጀር ርዕሰ መዲና ኒያሚ በተጀመረው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር÷ የአፍሪካ ሀገራት በመካከላቸው ያለው ንግድ እንዲስፋፋና የኢንዱስትሪ ልማቱ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ለዚህም የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ የግል ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን መዋቅራዊ መሰናክሎች ለማስወገድና ለማበረታታት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕቅድ ተግባራዊ ማድረጓን አስረድተዋል ።

ኢትዮጵያ የተሟላ አቅም ያላቸውና የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ 22 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ማካሄዷንና የትምህርት ስርዓቱ ለኢንዱስትሪ ልማቱ ብቃት ያለው የሰው ኃይል መፍጠር በሚያስችል ሁኔታ መቀረፁንም ገልፀዋል።

የአፍሪካ ህብረት ልዩ ስብሰባ ”የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማት ለአካታችና ዘላቂ የኢንዲስትሪ ዕድገትና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ማስፋት” በሚል ርዕስ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እየተሳተፈ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.